Translate

Wednesday, October 12, 2016

የጀርመን መራሂተ መንግስት አንግላ ሜርክል የኢትዮጵያ ጉብኝት




የሜርክል እና የሲቪክና ተቃዋሚ ድርጅቶች ውይይት

የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ዛሬ አዲስ አበባ ዉስጥ ከኢትዮጵያ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮችና ከተቃዋሚ  የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ጋር ተወያይተዋል።ዉይይቱ  በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካዊ ቀዉስና መንግሥት በሚወስዳቸዉ ርምጃዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር በዉይይቱ የተሳተፉት ገልፀዋል።


አርባ ደቂቃ ግድም የፈጀው ውይይት አንጋፋዎቹ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ፕ/ር በየነ ጴጥሮስን አሳትፎ ነበር፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ የጋዜጠኛ ማህበር ተወካይ፣ ጠበቃ እና ጦማሪ የተገኙበት ይህ ውይይት አብዛኛውን ትኩረት ያደረገው በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ እና መንግስት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ላይ እንደነበር በውይይቱ የተካፈሉ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል፡፡
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ እንደተናገሩት በውይይቱ ላይ ላለፉት 11 ወራት በሀገሪቱ እየተካሄደ ካለው ተቃውሞ አንስቶ ከትናንት በስቲያ በመንግስት እስከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድረስ ተነስቷል፡፡ በትናንትናው የምክር ቤት መክፈቻ ወቅት በመንግስት ቃል የተገቡ ለውጦችም የውይይቱ አካል ነበሩ፡፡
በአዲስ አበባ የጀርመን አምባሳደር መኖሪያ የተካሄደው ውይይት በኢትዮጵያ ባለው ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደነበር የሚናገሩት ተሳታፊዎች ሜርክል ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተው እንዳደመጧቸው እና ምላሽም እንደሰጧቸው ያስረዳሉ፡፡
ጀርመን በተለምዶ ከምትከተለው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ በዘለለ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊት እንድታደርግ በውይይቱ ተሳታፊዎች ተጠይቋል፡፡ ዶ/ር መረራ ጉብኝቱን ተከትሎ ከጀርመን እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገሮች ተጽዕኖ ይጨምራል ብለው ይገምታሉ፡፡
በአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተደማጭነት ያላት ጀርመን የመራሂተ መንግስቷን ጉብኝት ተከትሎ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠበቅ ያለ ጫና ታሳድራለች ተብሎ ተገምቷል፡፡ 
ተስፋለም ወልደየስ
ነጋሽ መሐመድ   

No comments:

Post a Comment